መጋቢት 12
ቅዱስ ሚካኤል
በዚች ቀን ቅዱስ ሚካኤልን እግዚአብሄር ወደ ጠንቋዩ በለአም
ላከው። እስራኤልንም ይረግማቸው ዘንድ ባላቅ በጠራው ጊዜ
አህያው በሰው አንድበት እስከ ተናገረች ድረስ አስደንገጠው
መርገሙንም ወደ በረከት መለሰው።
ከሚካኤል በቀር የሚያጽናናኝ የለም ( ትንቢተ ዳንኤል 10፤21)
ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ
«መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት
ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ -
የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት
ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው።
ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር
የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም
እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም
የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥
ክቡር ስም ነው።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን
ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ
እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት
መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት
ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት
መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ
አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦
«አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ
፹፭፥፰።
የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን
አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም
ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን
የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና
ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን ፡፡
ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ
በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ
ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ ፤
ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን
ወገን ነህ ? አለው ፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት
አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”(ኢያ.5፡13)
ይለናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ
ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር ፡፡
ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ
ዲያብሎስ ይዋጋው ፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር ፡፡
ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ
ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ
ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት
ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት”(ዘጸ.23፡21)ብሎ
አስጠንቅቋቸው ነበር ፡፡
ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን
ያስረዳናል ፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ
እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ
አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል
ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ
ገልጦልን እናገኛለን፡ሰይጣን ሠራዊቱን አሰማርቶ በአሕዛብ
ነገሥታት እያደረ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉ እስራኤልን
ዘወትር በጦርነት ያስጨንቃቸው ነበር።
በዚህም ምክንያት ሲወድቁ ሲነሡ፥ ሲነቀሉ ሲተከሉ፥ ሲፈርሱ
ሲገነቡ፥ ሲበተኑ ሲሰበሰቡ፥ ሲሰበሩ ሲጠገኑ ኖረዋል። በዚያ
ዘመን መጋቤ ብሉይ ተብሎ የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነው።
እርሱም ዘወትር ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ሆኖ ሕዝቡን ይረዳቸው
ነበርና።
ይኽንንም «ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህን?
አሁንም የፋርስን አለቃ እዋጋው ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም
ስወጣ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። (ሰይጣን በግሪክ
ንጉሥ አድሮ ሌላ ጦርነት ይጀምራል)። ነገር ግን በእውነት
ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ
(ከመላእክት አለቃ) ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም።» ዳን
፲፥፳፩ በማለት ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ለዳንኤል ነግሮታል።
ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ካለ እኛስ ምን እንበል?
+" ቅዱስ ድሜጥሮስ ድንግል "+
=>ቅዱስ ድሜጥሮስ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ:
በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው
ነበር:: በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ
ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት::
+ቅዱስ ድሜጥሮስ የነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን
በተክሊል ፈፀመ:: የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ
ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለ48
ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ: አንድ ምንጣፍና ልብስ
እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል::
+ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ
ክንፉን ለርሱ: ግራ ክንፉን ለርሱዋ ያለብሳቸው ነበር:: ከ48
ዓመታት በሁዋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የግብፅ 12ኛ ሊቀ ዻዻስ
ሆኖ ተሹሞ: ምስጢር በዝቶለት ባሕረ-ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል::
+ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ
ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልዐኩ
ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ: እሳት አስነድዶ: ከቅድስት ልዕልተ
ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል::
+ሕዝቡም ይሕን ተአምር አይተው: የቅዱሳኑን ንጽሕና
ተረድተው: "ማረን" ብለው በፍቅር የተለያዩት በዚሕ ዕለት ነው::
+ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን
በቅድስና አሳልፈዋል:: በተለይ ሊቀ ዻዻሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ
ድርሳናትን ደርሷል:: እነ አርጌንስ (Origen) ና ቀሌምንጦስ
ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ
መናፍቃንንም አውግዟል::
+ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኩዋ ምዕመናን
እየተበሰቡ ይማሩ ነበር:: በአልጋ ተሸክመውም ይባርካቸው
ነበር:: ቅዱሱ በ107 ዓመቱ ያረፈው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን
አጋማሽ አካባቢ ነው::
=>አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን:: ጸጋ በረከቱን
ደግሞ ያትረፍርፍልን::
ሰኞ 21 ማርች 2016
መጋቢት 12 በዓለ ቅዱስ ሚካኤል
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ