ማክሰኞ 5 ሜይ 2015

†††በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረቡት ጥያቄዎች†††(አዘጋጅ ሕሊና በለጠ ዘኖኆተ ብርሐን)


የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነገ ሚያዝያ 28 ቀን
2007 ዓ.ም. ይጀምራል፡፡ ነገ ለሚጀምረው ጉባኤ አባቶች
በአንድነት በዋዜማው (ዛሬ) ጸሎት ማድረሳቸው ሥርዐት ነው፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች
በአንድነት ከጸሎቱ በረከት በመሳተፍ ሲኖዶሱ ሊያያቸው የሚገባ
ጉዳዮችን አቅርበዋል፡፡ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ወጣቶቹ
ከየአጥቢያቸው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም
ገዳም በመሰባሰብ የአገልግሎት ልብሳቸውን ለብሰው ለሰዓታት
የአባቶችን መምጣት በጉጉት ሲጠብቁ ቆይተዋል፡፡
ብፁዐን አባቶቻችን ከየማረፊያቸው በአንድነት እስኪመጡ
ድረስም በቁጥር እጅግ ብዙ የሆኑትና ከብዙ አድባራት
የተሰባሰቡት የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አባቶችን በዝማሬ
ለመቀበል የሚያመች ሰልፍን በመሥራት በአንድነት እየዘመሩ
ቆይተዋል፡፡10፡30 ሰዓት አካባቢ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና
ብፁዐን አባቶች መምጣት ጀምረው ከደብሩ አገልጋዮች ጋር
በመሆን ጸሎትን በጋራ አደረሱ፡፡ የጸሎት መርሐ ግብሩ 11፡30
አካባቢ ከተጠናቀቀ በኋላ አባቶች ወደየማረፊያቸው
ከመመለሳቸው በፊት ሰንበት ተማሪዎቹ በአንድነት ጥያቄ አለንና
አባታችን ሊሰሙን ይገባል በማለት ጠየቁ፡፡ ሆኖም አንዳንድ
ይህ ዕቅበተ ዕምነት ያልተዋጠላቸው አካላትና ጥቅማችን
ይነካል ባዮች “ጉዳያችሁን በወረቀት አስገቡና ሒዱ” በማለት ያ
ሁሉ ወጣት ያን ሁሉ ሰዓት ጸንቶ መጠበቁን ገደል ሊከቱት
ሞከሩ፡፡ ነገር ግን ሰንበት ተማሪው በአንድነት መነበብ አለበት
በሚል ስለጠየቀ ይህንን የተመለከቱት ፓትርያርኩም ቶሎ
እንዲነገራቸው ፈቅደው እዛው በቆሙበት ወጣቶቹ ጉዳያቸውን
አቀረቡ፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነቱ ያቀረበው ጥያቄ በዋናነት
አምስት ነጥቦችን የያዘ ሲሆን በሰባት ገጽ ተጠቃሎ ቀርቧል፡፡
አምስቱ ዋና ዋና ነጥቦችና የደብዳቤው ዋና ዋና ይዘት
የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመሆናቸው እና ሕገ
ቤተክርስቲያንንና ቃለ አዋዲን የሚጻረር አፈጻጸም መኖሩ፤
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ሥር ሦስት ሐሳቦች በዋናነት ተዘርዝረዋል፡-
(ሀ) ጥፋተኛ ተብለው በሕግ እንዲጠየቁ የተወሰነው ውሳኔ
ፍጻሜ አለማግኘቱ፣ ኑፋቄን በማሰራጨት ማስረጃ የቀረበባቸው
አካላት ጉዳይ በእንጥልጥል መቅረቱና ከቤተክርስቲያን ሥርዐት
ውጪ ራሳቸውን አጥማቂ ብለው ስለሚያጠምቁ ግለሰቦች
የቀረበው ማስረጃ እልባት አለማግኘቱና የተወሰኑ ውሳኔዎችም
አለመተግበራቸው፤ (ለ)ጥቅምት21፣2007ዓ.ም. በተደረገው
ስብሰባ በአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ላይ የተወሰነው ውሳኔ
በሌላ ደብዳቤ መሻሩ፤ (ሐ)በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ
አስኪያጆች ሹመት ምክንያት የደብዳቤ ልውውጦች ላይ የሕገ
ቤተክርስቲያን ጥሰት መኖሩ፤
2.ራሱን “የተሐድሶ አራማጅ” እያለ የሚጠራው ቡድን
በቤተክርስቲያን ውስጥ በኅቡዕ ከውጪ ካሉት መናፍቃን ጋር
በመተባበር ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ኃይል
መኖሩ፤
በዚህ ርእስ ሁለት ጉዳዮች ተነሥተዋል፡-(ሀ)ከዚህ ቀደም
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማስረጃ ያቀረቡባቸው ጉዳዮች ከፊሎቹ
ውሳኔ ቢያገኙም ከፊሎቹ በእንጥልጥል መቅረታቸው፤ (ለ)
በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን መካከል
አንዳንዶች ባልታወቀ ምክንያት እንዲመለሱ መደረጋቸውና ስም
በመቀየር መልሰው ሥራ የተቀጠሩ መኖራቸው እጅግ አሳሳቢ
መሆኑ፤
3.ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በልዩ ልዩ መድረኮች ባደረጓቸው
ንግግሮች እና እኛም በኅብረት ከእሳቸው ጋር በተወያየንበት
ወቅት ሙስናን ከቤተክርስቲያን እንደሚያጠፉና እንደሚዋጉ፣
የቤተክርስቲያንንም የቀድሞ ቅድስናዋን፣ ልዕልናዋን፣ ክብሯን
እንደሚያስመልሱ በተደጋጋሚ የገለጡ ቢሆንም እስካሁን
ምንም የታየ ለውጥ ባለመኖሩና ችግሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ
እየባሰ መምጣቱ የሚከተሉት ነገሮችን አስከትሏል፡-(ሀ)አንዳን
ድ የሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፣
ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች በጉቦ በዝርፊያ መሰማራታቸው፣
በአግባቡም ሥራቸውን አለመሥራታቸውና በሥራ ቦታ
አለመገኘታቸው እና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ምዝበራ መኖሩን
የሚያረጋግጡ ነገሮች እንደ አሸዋ የበዙ መሆናቸው፡፡ በዚሁ
ተግባር የተሠማሩ አካላት የሚያገኙት ካላቸው ቤት፣ መኪናና
ኑሮ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ በአቋራጭ ተገቢ ባልሆነ
ሁኔታ የበለፀጉ መሆናቸውን በማያሻማ መልኩ የሚያረጋግጥ
ነው… (ለ)ሥራ ቦታቸው የማይገኙ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች
መኖራቸው ደመወዛቸውንም እንኳ በተልእኮ የሚቀበሉ ኃላፊዎች
በመኖራቸው በየአጥቢያው ላይ ብጥብጥና ችግር እያስከተለ
በመሆኑ… (ሐ)በአንዳንድ አድባራት የሀብታም ልጆችና የድሀ
ልጆች ብለው በመለየት ከፋፍለው ትምህርተ ሃይማኖት
እናስተምራለን የሚሉ ግለሰቦችና ኃላፊዎች መኖራቸው፤
4.እውነተኛ ፍትሕ አለመኖሩ፤
በቤተክርስቲያን ውስጥ አጥፊው የሚሾምበት፣ መልካም ሠሪው
የሚታገድበት፣ በጥፋታቸው የተጎዱት ደግሞ ያለ አግባብ
የሚመለሱበት፣ የጎጠኝነትና የዘረኝነት አሠራር የመሳሰሉት
ነገሮች መንሠራፋታቸው ለአገልግሎት ትልቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም ይህ ተግባር የሚታረምበት አሠራር ይዘረጋ ዘንድ
እንጠይቃለን፡፡
5.አንዳንድ የአጥቢያ አስተዳደር ኃላፊዎች የሰንበት ትምህርት
ቤት ወጣቶችን ማዋከብ፤
አንዳንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች በምንፍቅናና በሙስና ውስጥ
የተዘፈቁ በመሆናቸው ይህን ጉዳይ ሊያጋልጠን የሚችለው
ደግሞ የሰንበት ተማሪው ነው ብለው ስለሚያስቡ ከሰንበት
ተማሪዎች ጋር በመጋጨትና የተቀመጡበትን የቤተክርስቲያን
ኃላፊነት ያለ አግባብ በመጠቀም የሰንበት ትምህርት ቤት
ወጣቶችን በማሣሠር ብሎም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ
ከመንግሥት ጋር ለማጣላት ሽብርተኞች ናቸው፣ መንግሥትን
ለመገልበጥ አሲረዋል፣ በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች ወጣቶችን
በማዋከብ ላይ መገኘታቸው እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር
ከአንድ መንፈሳዊ አባትም የማይጠበቅ ነው፡፡
በመጨረሻም እነዚህ በስፋት ተንሰራፍተው የሚገኙ አሳፋሪ
ድርጊቶች አንገታችንን የሚያስደፉ ሆነው ሳለ አይተን እንዳላየ፣
ሰምተን እንዳልሰማን ማለፍ ሃይማኖታችንም ሆነ ሕሊናችን
የማይፈቅድ በመሆኑ፣ ብሎም በእግዚአብሔር የሚያስጠይቀን
በታሪክ የሚያስወቅሰን ስለሆነ ጥያቄዎቻችንን ለማቅረብ
ተገደናል፡፡ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችም መፍትሔ ለመስጠት
የሚቸገሩ መሆናቸውን የተረዳነው ስለሆነ ነገሮች ተጠራቅመው
አቅጣጫቸውን ስተው ወደአልተፈለገ ሁኔታ ከመሔዳቸው በፊት
እጅግ በጣም ስላሳሰበን እልባት እንዲሰጣቸው የቅዱስ ሲኖዶስ
አባላት በትኩረት እንዲያዩትና ውሳኔ ያሳልፉ ዘንድ በአክብሮት
እንጠይቃለን፡፡
“የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚጋፋ ማንኛውንም አሠራር
እንቃወማለን”
“የመናፍቃንንም ሴራ እንታገላለን”
†††
ደብዳቤው በዋናነት የተጻፈው ለቅዱስ ሲኖዶስ ሲሆን
በግልባጭ ለጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ለአዲስ አበባ
ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት፣ ለአዲስ
አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር
ቢሮ ለደኅንነት አማካሪ፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
የሃይማኖት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት፣ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት
አገልግሎት፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣
ለአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
በሰባት ገጽ የቀረበውን የደብዳቤውን ሙሉ ይዘት ከሚከተሉት
ምስሎች ማግኘት ይችላሉ፡፡
የአባቶቻችንን ጉባኤ እግዚአብሔር ይባርክ፤
ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን፤

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ